ምንድነው ዕንቆጳዊነት መቸስ ነው የእንቆጳ ትንሳኤ ? (አሌክስ አብርሃም)

ምንድነው ዕንቆጳዊነት መቸስ ነው የእንቆጳ ትንሳኤ ?
(አሌክስ አብርሃም)

ከሰሞኑ <<ዕንቆጳዊነት>> የሚል ሃሳብ መጀመሬ ይታወቃል ! በርካታ የፌስቡክ ወዳጆቸም ዕንቆጳዊነትን በገባቸው ልክ አልያም በራሳቸው በሰጣቸው ስሜት ልክ እየተቀባበሉት ይገኛሉ ! አንዳንዶች በጉዳዩ ላይ ሲያላግጡ ሌሎች ደግሞ ድግግሞሹ አስልችቷቸው አዲስ ጨዋታ አምጣ ሳምንቱን በዕንቆጳ ከረምክብን እያሉኝ ነው ! ከሆነስ ሆነና ምንድነው ዕንቆጳዊነት ? ማናትስ ዕንቆጳ ? የእንቆጳ ትንሳኤስ የእውነት ያስፈልገናል ወይ ? እነሆ እንቆጳዊነትን የጀመርኩበት ሃሳብ !

በክቡር ዶ/ር ደራሲ ሐዲስ አለማየሁ ከ 50 ዓመታት በፊት የተደረሰው ፍቅር እስከመቃብር መጽሃፍ ለብዙሃኑ ኢትዮጲያዊ ከልብወለድነት ያለፈ ትርጉም ያለው መጽሐፍ ነው!ያነበበውም ያላነበበውም ፍቅር እስከመቃብርን ያውቀዋል !! በዚህ መጽሐፍ የተፈጠሩ አይረሴ ገጸባህሪያት የአንድ ኢትዮጲያዊ የስጋ ዘመድ እንጅ ምድራችን ላይ ያልነበሩ የፈጠራ ገጸባህሪያት እስከማይመስሉ ተዋህደውናል!!

ከነዚህ ገጸባህሪያት አንዱ ጉዱ ካሳ (ካሳ ዳምጤ ) ነው! ጉዱ ካሳ ጉድ ከፊቱ ቀድሞ መጠሪያው የሆነው የማህበረሰቡን ጉድ ሳይፈራ ስለሚነቅፍ እና ከዘመኑ ወግ ባህልና ጎታች አስተሳሰብ ወጥቶ በወቅቱ ክነበርው ማህበረሰብ ያፈነገጠ ባህሪ ስለተላበሰ ነበር!! እንግዲህ ጉዱ ካሳ በናቱም ባባቱም ከባላባቶች የተወለደ <<በሁለት እጅ የማይነሳ የጌታ ዘር >> ነበር! ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ የሆነለት !! ምን ይሄ ብቻ በዘመኑ የቤተክህነት እውቀት የመጠቀ ሰው ነበር! ታዲያ እውቀቱ ተጨምሮበት ይቅርና ከወቅቱ ባላባቶች የዘር ሃረጉ በመመዘዙ ብቻ ስልጣን እና ወንበር ቢፈልግ ኖሮ የትየለሌ ይደርስ የነበርው ሰው ስልጣኑንመ ባጥንትና ዘር ያገኘውንም ክብር ጣጥሎት ማህበረሰቡን በትችት የሚያሽቆጠቁጥ ከባላባት እስከተራ ሰው ልክ ልካቸውን የሚነግር <<ጉድ >> ሆነባቸው! የሚኖርበት ማህበረሰብ በእውቀትና ማስተዋል ለገዘፈ እሱ ጠበበው ! የጠበበውን ማህበረሰብ አውልቆ ጥሎ በራሱ ዓልም በእርቃን ብቸኝነቱ ሲኖረ ማህበረሰቡ እብድ አለው ! ጉድ አለው!

ጉዱ ካሳ የሚኖርበት ማህበረሰብ ወግ ፣ህግ ና ስርዓቱ <<የማይረባ>> መሆኑን <<የማይጠቅም>> መሆኑን ይሰብክ ጀመረ! ይህን አሮጌ የበሰበሰ ስርዓት እንደእግዚአብሔር ቃል ሳይሻሻል ተከብሮ እንዲኖረ የሚጣጣሩትን የልማድ ባሮች ሁሉ <<ከብቶች>> <<ድንጋዮች>> እያለ ይዘልፍ ነበር!! እንዲህ ሲል
(((((“የማኅበራችን አቁዋም የተሠራበት ሥራት፣ ልማዱ፣ ወጉ፣ ህጉ እንደ ሕይወታዊ ሥራት ማኅበር ሳይሆን ሕይወት እንደ ሌለው የድንጋይ ካብ አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርቦ የላይኛው የታችኛውን ተጭኖ የታችኛው የላይኛውን ተሸክሞ እንዲኖር ሆኖ የተሠራ በመሆኑ ከጊዜ ብዛት የታችኛው ማፈንገጡ ስለማይቀርና ይህ ሲሆን ሕንጻው በሙሉ እንዳይፈርስ እንደገና ተሻሽሎ፣ ሰውን ከድንጋይ በተሻለ መልክ የሚያሳይ የሕያዋን አቁዋመ ማኅበር እንዲሠራ ያስፈልጋል” ))))

ታዲያ እንዲህ በቁጭት ለተጨቆኑት (ለታችኞቹ ድንጋዮች ) ሲናገር <<አይ መበላሸት አይ መማር ከንቱ አይ የትልቅ ሰው ልጅ እያሉ ያዝኑለት ነበር!! እሱም በዛ በማይረዳው ማህበረሰብ ውስጥ ሰሚ የሌለው ጩኽቱ ወግና ባህል ያጠጠረው ተራራ ማህበረሰብ ጋር ተጋጭቶ ወደራሱ ሲመለስ ያዝንና ይበሳጭ ነበር!!ጉዱ ካሳ የሚናገርው ለማህበረሰቡ አይጥም ህብረተሰቡ የሚናገረው ለሱ አይጥመው ሀዝቡ እሱን <<ጉዱ>> እሱም ማህበረሰቡን <<የጫኑትን ተሸክሞ የሚግተለተል እንስሳ <የጉድ ማህበር >> እያለ አብረው ይኖራሉ !!

ይሄ በማህበረሰብቡ <<ጉድ>> የሆነ ጉዱ ካሳ ይህን ሁሉ ጉድ አልበቃው በሎ በመላስ የሚወጋው በድንዛዜ ባለማወቅ የሚወጋው ማህበረሰብ ጋር ጦር አውርድ የሚያስብል ሊላ ጦር ሰበቀ ! ይሄንኛው ጦረ ጭራሽ ዘመድ አዝማዱን <<አንገት ያስደፋ >> ማህበረሰቡም <<ለየለት>> በሎ በደንብ ይለየው ዘንድ የሚያደርግ ሆነና የጉዱ ካሳ ወትሮም የሌለ ማህበራዊ ሕይዎት ቀጭን ክሩ ተበጥሶ ማረፊያ ወደሌልው የባህል ገደል ገባ ! ምን አደረገ ? በወቅቱ አጠራር <<ባሪያ>> በሽልማት ተሰጠው ! የጥቁረቷ ነገር አይወራ ጸሃይ ዘወር ካለ አይንና ጥርሷ በቻ መነፈስ ላይ ብቻውን የተገጠመ መስሎ ይንቦገቦጋል እንጂ እሷ አትታይም ! <<ባርነት>> ለተባለ የመሃበረሰብ ክፉ እምነት እግዜር ተስማመቶ በጥቁር ቀለም ነክሮ ያጠመቃት የመሰለች የእኩለሌሊት ጨለማ !!

ለጉዱ ካሳ ተሰጠች! እግሩን እንድታጥብ ሲያገባ ለሚስቱን ጠብ ርግፍ ብላ እንድትገረድ ውሃ እንድትቀዳ እንጀራ እንድትጋግር እና ደግሞ ከፈለገም ወንድነቱ ካሰኘው በፈለገው ሰዓት ወደአልጋው ሊጎትታትም ይችላል <<ባሪያ ናት ሰው አይደለችም>> ለምሳሌ ውጭ በሌላ ነገር ተበሳጭቶ ሲመጣ እልሁ አልወጣ ቢለው ባገኘው ብትር እንደስልቻ ሊወቃትና እልሁን ሊያበርድባት ይችላል ከሞተችም ወይኔ ድብደባየን ሳልጨርስ ሞተች የማትረባ በሎ ሊቆጭ ይችላል ! <<ባሪያ ናታ ሰው አይደለችም>> ከወለደች ልጆቿም እሷም እኩል ባሪያ ናቸው!!

ጉዱ ካሳ ማህበረሰቡ <<ጨዋ የጨዋ ዘር የሆነች ደርባባ እመቤት አግብቶ በሚስቱ ግፊት <<ሰው ይሆናል >> ብሎ ሲጠብቀው እንቆጳን በደንቡ በወጉ ሚስቱ አድርጎ አገባት!! ያኔ እንኳን <<ጨዋው >> ማህበረሰብ <<ባሪያዎቹ >> ራሳቸው <<ኤዲያ አሁንስ እኒህ ሰውየ አበዙት ጭራሽ ባሪያ ያግቡ>> ሳይሉ አይቀሩም !! የማይታሰብ የማይሞከር ነዋ! እንቆጳ የጉዱ ካሳ ሌላ ህጋዊ ጉድ ሆነች ! ማህበረሰቡ ግን ጋብቻቸውን ማመን አልፈለገም !! እንቆጳ በገበያ የምትገፋ፣ ውሃ ልቅዳ ብትል እንደሳምራዊቷ ሴት አሳቻ ሰዓት ጠበቃ ወንዝ የምትወርድ፣ አገር ምድሩ ያሳቀቃት ከጓዳዋ ውጭ ሰው መሆን የከበደባት የባህል ጉድ የተሸከመች የጉድ ሚስት ሆነች! እንደሰባራ ቅል ካሁን ካሁን አውጥቶ ወረወራት ተበሎ ሲጠበቅ ትዳራቸው ጭራሽ አምሮበት ለጅ ለማፍራት በቁ ! የእንቆጳ ትልቅ ህመም የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው ሁለቱም ልጆቿን ሞት ነጠቃት ! ሞቱ የተፈጥሮው ሞት አልነበረም <<ከባሪያዋ እንቆጳ ዘራችን እንዳይቀጥል ዘር እንዳይበላሽ >> በሚል ሰበብ ምንም የማያውቁ ሀጻናት ለቆሸሸው የባህል ጣኦት መስዋዕት ሆኑ ! በምን ገደሏቸው ? ቢባል ብርቱው ጉዱ ካሳ ሳይቀር <<ጥላ ወጊ ነው ይላሉ ማመንም አለማመንም ከባድ ነው !! >> ብሎ ዝም ይላል!!

እንቆጳዊነት ግን በምድሪቱ ወርድና ሰፋት የዘር ርሾውን ፣ የገፊና ተገፊ ቡኮውን አገር ምጣድ ላይ እየጋገረ ሚሊየኖችን በሰው ደም በሌሎችም መሸማቀቅና ሰቆቃ ላይ የግፍ ምድር ይገነባል ! ጦሱ ብቻ ኣይደለም ራሱ ምከነያቱም ዛሬም አብሮን ተደላድሎ ተቀምጧልና እንቆጳዊነትን ሳይነቅሉ የበቀለበትን አኬልዳማ ምድር በመከባበር በፍቅርና እኩልነት ሳያርሱ ፍቅር ልዝራ ማለት ዘበት ነው ! እና እንቆጳዊነት ጥቁረት ነው? ዘር ነው? ቋንቋ ነው? ምንድነው? በየት በኩል ነው እየገፋ ገደል አፋፍ ሊያደርሰን የሚያቻኩለን?

ይህች ገጸ ባህሪ ከዘር በወረሰችው ባርነት ለዘላለም ባሪያ ሁና እንድትታወስ ጉዱ ካሳ ለተባለው ገጸ ባህሪ ብትሰጥም በባርነት የተበረከትችለትን ሴት በሚስትነት ተቀብሎ አገባት ማህበረሰቡ እሷንም እሱንም አገለላቸው! ጉዱ ካሳ ሰሚ ኖረውም አልኖረውም ተናጋሪ ነው ! ሀዝቡን ሲያሻው <<ከብት>> ይለዋል! በል ሲለውም ድንዛዜው የገባው ዘንድ <<ድንጋይ>> ይለዋል ! እንቆጳ ግን በደሏን ዋጥ አድርጋ ማህበረሰቡ ያሳረፈባትን የባህል እና አጉል እምነት ዱላ ችላ በጓዳ እንደኖረች በጓዳዋ ሞተች ! እንቆጳ ጠንካራ ሴት ነበርች ፣ እንቆጳ ቆንጆ ነበርች ግን ደግሞ ጥቅጥቅ ያለ እንደጨለማ ይሚያስፈራ ጥቁረት ! በጥቁረቷ ውስጥ ውበቷ በጓዳዋም ውስጥ ሰውነቷ እንደተቀበረ አለፈች! እንቆጳ ሚሊየኖችን ናትና ሰለሚሊየኖች መገፋት እንጮህበት ዘንድ ስሟን መነሽእችን አድርገነዋል!! <<እንቆጳዊነት>>!!

እንቆጳዊነት ብየ የሰየምኩት የሰሞኑ ሃሳቤ ምንድነው ምንስ ይፈይዳል የሚለውን እናያለን!
ሰዎችን በዘራቸው፣ በውጫዊ መልካቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በሙያቸው ባመለካከታቸው ፣ በጾታቸው (በተለይ ሴቶችን ) ወይም በተፈጥሮም ይሁን በአደጋ ሰውነታቸው ላይ በሚደርስ ጉዳት ማግለል የአገራችን የተድበሰበሰ እውነታ ነው! እንቆጳዊነት ደግሞ መሃበረሰቡ ለማግለል በሚጠቀምባቸው ወግና ልማዶች እንዲሁም ህግጋት ታፍኖ መኖር ነው! ቢቻል ማንኛውም አፋኝ መንገዶች ተቋቁሞ ሰው መሆነን ፣ አልያም ይህን የማህበረሰብ አይን ያወጣ ግፍ ተቋቁሞ እኩል በተፈጠሩባት ምድር አንሶ ዝቅ ብሎ መኖር ይህንንም ለልጅ ማውረስ ነው!!ባጠቃላይ እንቆጳዊነት በተፈጥሮ የተሰጠን ሰው የመሆን ጸጋ በሰዎች መነጠቅና እሱን ለማስመለስ መታገል ነው!

የእንቆጳዊነት አላማ እንደሰው እኩል ከሰው መኖርን የማረጋገጥ አካላዊም ይሁን ስነለቦናዊ ብርታት ነው!! ማህበረሰቡ ካስቀመጠብን ጨለማ መውጣት ነው ! ተፈጥሯችንን በግፊት ለመቀየር ከመጣር ይልቅ ሁነን ከነተፈጠርነው አካላዊ ምንነትና ሰነልቦናዊም ማንነትጋ ተቀባይነት ማግኘት ነው! በማንኛውም መንገድ በየትኛውም አስገዳጅ ሁኔታ በግፍ የተቀማ ሰበዊነትን ፣ በጉልበት የታገደ ሃሳብን ፣ በባህልም ይሁን ህግ የታጠረ መገፋትን የመቀበል ስነልቦና አሽቀንጥሮ መጣል ነው !!

በዓለማችን ላይ በየትኛውም ሁኔታ የተነሱ የነጻነት ትግሎች የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ <ሜካፕ>ቢጠቀሙም ቅሉ መነሻቸው የበላይ የመሆንና የበላይነትን ያለመቀበል የሰዋዊ ፍላጎት ግጭቶች ናቸው!! ወደኛው አገር ስንመጣም የሚያኮራ የምንለው ባህል ታሪክ ቢኖረንም ቅሉ እጅግ አሰቃቂ እና አሳፋሪ እንዲሁም እንደሰው ተቀባይነት የሌለው ብዙ ልምድ ያለብን ህዝቦች ነን!!የሚያሳዝነው ዘመኑ እየሰለጠነ ሲሄድ እኛ እየባሰብን ይሄው በግለሰብ በየሰፈሩና በየጓዳው የምንሰነዝረው በዘር ፣ በቋንቋ ፣ በቆዳ ቀለም በተፈጥሮ መልክ ይምንፈጽመው ማግለልና ፍርጃ ዛሬ ዙሮ አገር ሊያፈርስ ደም ሊያፋስስ በራችን ላይ እየተንጎማለለ ይገኛል ! << ፖለቲካ >> ክሚባለው ፍልስፍናና አመለካከት ወጥተን እንዲሁ ማህበራዊ ህይወታችንን ስንመለከትው ባደገኛ የማግለል እና የመፈረጅ ነቀርሳ የተመታ በሽተኛ ኑሮ መስርተን በዛው በሽተኛ ጭስ እየታፈንን ነው!

ሌላው ዝርዝር ይቆየንና አሁን እንኳን በአገራችን ፖለቲካ ምንድነው ከዳር እዳር የሚያንጫጫን ? የኔ ብሔር ተገለለ የእከሌ ብሔር እኔን አግልሎ ተጠቀመ የሚል ቅሬታ ነው አይደል ? ምንድነው የሚያባላን ብሔሬ ተናቀ ተሰደበ ተፈረጀ የሚል ቁጣ አይደለም እንዴ? የሁሉም መነሻ ግለሰብ ነው . . . የግለሰብ ስድብ አድጎ የብሔር ስድብ ብሎም የአገር ስድብ ይሆናል! በብዙ አመለካከትና በብዙ ፍልስፍና ታሽቶ ደልቦ ስናየው ተዓምር ይመስለናል እንጅ የአገር ስድብ የኛው የግለሰቦቹ የጓዳ ስድድብ መዋጮ ውጤት ነው !

ለመሆኑ እንደማህበረሰብ ጨዋ ነን ወይስ ባለጌ ?

እንቆጳዊነትን ስንደመድመው !!
እንደህዝብ ባለጌ ነን ወይስ ጨዋ ?

እኛ ኢትዮጲያዊያን እንደሚባለው” በጋራ የምንበላ በጋራ የምንጠጣ” ህዝቦች ብቻ ሳንሆን በጋራ ሰዎችን ማግለል በጋራ ሰዎችን ያውም አቅመደካሞችን የምናጠቃ ህዝቦችም ነን!ማጥቃት ሲባል ጦር መዞ ሰው ላይ መዝመት ብቻ አይደለም፣ እሱማ ግልግል ነው ! ወይ መሞት ነው አልያም መቁሰል ነው ! እኛ ግን እድሜ ልክ በደም ስር ውስጥ እየተዘዋወረ እንደቅንቅን ሌሎችን በልቶ እኛንም የሚያጠፋ ክፋት ተዘርቶብናል !! ለዚህ በደላችን እንዲመቸን ያላሰመርነው መስመር ያልደነገግነው ህግ ያላላመመድነው አይነት ባህል የለም !! እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ውስጥ እከሌን ከከሌ ሳይለይ የክፋት ዘር ተዘርቶበታል! ይሄ በደፈናው ህዝብን መውቀስ ደሰ አይለንም ግን ደግ ተፈጥሮ ያለው ኢትዮጲያዊ እንኳን ቢኖር የሚያድገበት ማህበረሰብ ውስጥ እየተጋተ ያደገው የደግነትም ይሁን ክፋት ወራሽ ነው!!

ህዝባችን የለየለት ተሳዳቢ ነው ! የተማረው ቢባል ያልተማረው ሴቱ ቢባል ወንዱ ትንሹ ትልቁ ሃይማኖተኛው ሃይማኖት የለሹ ባንድም በሌላም መንገድ ስድብ ደሙ ውስጥ አለ ! ይህ ባህል ከየት እንደመጣ ማን እንዳወረሰን ባናውቅም መጥፊያችን ለመሆኑ ግን አትጠራጠሩ !! እንደውም ስድብን እንደባህል የያዘ ማህበረሰብ የተትረፈረፈባት አገር ባለቤቶች ነን! አስከፊው ነገር ደግሞ የስድቦቹ ይዘት ሰዎችን ሆነ ብለው በመልካቸው ፣ በዘራቸው ፣ በተፈጥሯቸው ፣ በጾታቸው የሚያሸማቅቁ ፣ የሚያገሉ ሰዎች በስነልቦና ተንኮታኩተው እንዲወድቁ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው! እነዚህ ሰዎች እንደምንም ይህን ጫና ተቋቁመው ተለቅ ደረጃ ቢደርሱ እንኳን በቀለኞች ጨካኞች እና ለማህበረሰባቸው ሃይለኛ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ነው የሚሆኑት !!

ለዚህ ጽሁፌ መነሻ ሁላችንም የምናውቀውን አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ልስጥ ! በቅርቡ ከስልጣን የወረደው የሱማሌ ከልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር በታላላቅ ሚዲያዎች ሳይቀር (((አብዴኢሌ))) ተበሎ እንደሚጠራ ታውቃላችሁ! እናተም ብዙ ጊዜ በዚሁ ስም ጠርታችሁት ይሆናል !ይታያችሁ ይህ ሰው አሁን ላይ ሰታስቡት ለብዙ ሰዎች ሞት መቁሰልና መፈናቀል ምክንያት የሆነ ሰው በመሆኑ በቁጥጥር ስር ወሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው! ከዚህ ሁሉ በፊት ከስልጣኑም በፊት የተለጠፈበትን ስም ትርጉም ስትሰሙ ግን ማህበረሰቡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ምን ያህል አሸማቃቂ ስም በግለስቦች ላይ እየለጠፈ ሰዎች ስድባቸውን ተሸክመው አቀርቅረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ባህል እንዳለው ትረዳላችሁ !

የአካባቢው ነዋሪ የሆነ የዩኒቨርስቲ መምህር ፌስ ቡክ ላይ ባሰፈረው አንድ ጽሁፉ እንዲህ ይለናል
(((((አብዲ መሀሙድ ኡመር ለምን አብዲኢሌ እየተባለ ይጠራል?
አብዲኢሌ አጠር ብሎ ነው እንጂ አብዲ ኢነ ኢሌ ነው ስሙ። እነ ኢሌ ማለት የኢሌ ልጅ ማለት ነው። ኢሌ ማለት አይነሸውራራው ማለት ነው። ሶማሌ ቅፅል ስም በአካላዊ ሁኔታ የማስቀመጥ የቆየ ባህል አለው። የሚያነክስን ጂስ (አንካሳው) አፈጠማማን (አፍቀሎኤ) አፈጠሞ እያለ ነው የሚጠራው። ስለዚህ አብዲኢሌ ማለት አብዲ የሸውራራው ልጅ ማለት ነው። ምንም ነውር የሌለበት የቅፅል ስም አሰጣጥ ነው። )))

ይህን ነገር ከሌሎችም የሱማሌ ተወላጅ ጓደኞቸ ጠይቄ እንደተረዳሁት እውነት ነው ! ሰዎችን በተለይም በካላዊ ገጽታቸው ላይ ባለ እንከን መጥራት ቅጽል ስም ማውጣትም በበዙሃኑ የሱማሌ ህዝብ ዘንድ <<ምንም ነውር የሌለበት >> ባህል ነው !! ሁላችንም በምናውቀው ምሳሌ ለመነሳት ያህል እንጅ የትኛውም የአገራችን ክፍል ብትሄዱ አጥንት የሚሰብሩ ስድቦች በመሃበረሰቡ ውስጥ እንደቀልድ የሚወረወሩ <<መዝናኛዎች>> ናቸው! በሔርን ጠቅልሎ ከመስደብ አልፎ በግለሰብ ላይ እያንዳንዱ ሰው ቢጠየቅ ልቡ ውስጥ ከማህበረሰቡ የተበረከተለት ስድብ በክብር ተቀምጧል! ምንም ብትሆ ትሰደባለህ ! ውፍረት ያሰድባል ክሳት ያሰድባል . . . ቅላት ያሰድባል ጥቁረት ያሰድባል ፣ መርዘም ያሰድባል ፣ማጥር ያሰድባል ፣ ሁሉም ነገር ያሰድባል ሌላው ሁሉ ይቅርና ዝምተኛ መሆን ያሰድባል ተናጋሪም መሆን ያሰድባል !

እኔ ሶስተኛ ክፍል እንደነበርኩ የክፍላችን ጎበዝ ተማሪ የነበረ ልጅ አስተማሪዎቻችን ሳይቀሩ <<እንትና ጥርሶ>> እያሉ ሲጠሩት ትዝ ይለኛል ! በዛ የህጻንነት እድሜ ባወራ በሳቀ ቁጥር ትንንሽ መዳፎቹ አፉን በመሸፈን ይጠመዱ ነበር ! ሃይስኩል ስንገባ ያ ልጅ ከአፉ ላይ ስካርቭ ተለይቶት አያውቅም !ልክ ስታይል በሚመስል መንገድ ከራስህ ህብረተሰብ ያንተ ጥፋት ባልሆነ ነገር የራስህ እስር ቤት ውስጥ እንዲህ ትኖራለህ ! ቀዮችን ሰላቶ ፣ አይናቸው ትንንሽ የሆኑ ለጆችን ጩኒ ቻይና ፣ የሚያነክሱ ልጆችን ኮካ ፣ ጸጉራቸው ከርዳዳ የሆኑትን ኪሚኪ ቁጭራ ፣ ወፍራሞችን ዱብየ ፣ አጭሮችን አጭሬ ድንክ ፣ ረዥሞችን ቀውላላ ፣ ከዚህም አልፎ ከንፈራቸው ትልልቅ ልጆችን ሰፊ አፍ ፣ አፍንጫቸው አጭሮችን ጎራዳ ፣ የእራሳቸው ቅርጽ ያልተስተካከለ ልጆችን ገንቦየ ፣ጆሯቸው ቆም ያሉትን ማንትስ ጆሮ ፣ እግራቸው ወይም እጃቸው የተቆረጡትን ቆማጣ ዱሽ ፣ አይነስውሮችን እውር . . . ሌላው ይቅርና ሴቶች ልጆች ጡታቸው ማደግ ሲጀምር እዚህ ላይ ልደግመው የማልፈልገው ስድብ አብሮ አእምሯቸው ውስጥ እንዲያድግ ይደረጋል ! ለዛም ነው ጡታቸው ብቅ ባለ ቁጥር እጅ በደረት አድርገው በሰቆቃ ተፈጥሯቸው ጋር ጦርነት ይገጥማሉ ! በነገራችን ላይ የትም ሂዱ ኢትዮጲያዊያን ሴቶችን <<ትህትና>> በሚል የዳቦ ስም ሲሸማቀቁ አለም ሁሉ እነሱን የሚያያቸው ሲመስላቸውና ካነጋገር እስካረማመድ ነፍሳቸው በሰቆቃ ሲታመስ ታውቋቸዋላችሁ ! (ብዙዎቹ ራሳቸውም አይታወቃቸውም)

ማህበረስቡ እድሚያችሁን እየተከተለ ሀመሙም የሚያድግ ስድብ ይጨምርላችኋል አንዲት ሴት ሳታገባ ብትቆይ ቁሞ ቀር ፈላጊ የሌላት ፣ አግብታ ብትፈታ ጋለሞታ (በነገራችን ላይ ጋለሞታ በድሮ ጊዜ ጥቅም ላይ የማይውል የተሰነጠቀ ምጣድ አልያም የሸክላ ድስት እንደማለት ነበር አሉ) እንግዲህ ምክንያቱ ምንም ይሁን ከተዳሯ የተፋታች ሴት ባሏ ሙቶ እንኳን ቢሆን ጋላሞታ መባሏ አይቀሬ ነው !!

ከፍ ስንል ደግሞ ይሄን ሁሉ ስድብ እየተሞላ ያደገው ዜጋ ባንድ ላይ ሁኖ ለሌላው ብሔር የስድብ ስም ያወጣል ተሰዳቢው ብሔርም በስድብ ይመልሳል ! ይሄ ሁሉ ሁኖ <<አገሬ ተሰደበች >> በሎ ደግሞ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ትመለከቱታላችሁ ! ይህ የስድብ እና የማግለል ነገር በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም ዘር መዞና አጥንት ቆጥሮ አንዱን ባሪያ ሌላውን ጌታ ፣ አንዱን የሃብትና ስልጣን ባለቤት ሊላውን የበይ ተመልካች ሲያደርግ ታያላችሁ ! በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ እያለን እንኳን ከዚህ የገንዘብም የ አእምሮም ድህነት እናውጣችሁ የሚሉ ፖለቲከኞቻችን ቁጥር ስፍር የሌለው አዳዲስ የስድብ ቃል እየፈበረኩ በለገናችንን ያድሳሉ ! አሽሙር ማንጓጠጥ በራሱ አንሶ ሌሎችን ማሳነስ መሆኑን እሳካሁንም ያልገባው ፖለቲካችን ዋናው የስድድብ መድረካችን ሁኗል !

ቆስለናል ፣ በስብሰናል ፣ በየሰፈሩ በየጓዳው ሚሊየኖችን በስድብ ፣ በዘር ፣ በሙያ በኑሮ ደረጃ በመልክ አግልለን ገድለናል ፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን አቀጭጨን አሳድገናል ! ሶሻል ሚዲያውን ማየት ብቻ ለዚህ በቂ ምሳሌ ነው ! እንግዲህ የእንቆጳዊነት ጽንሰ ሃሳብ በራሳችን ምላስ መገዳደል በተፈጥሮ ባገኘነው መልክ ፣ዘር ፣መገፋፋት ከምንም በላይ ግን ግለሰቦችን በቃልም ሆነ በድርጊት ማግለል ከለባችን እንጸየፍ ነው !! ጨለማችን ይብቃ ነው ! ጥቁረት ውስጥ ቁንጅና እንዳለ ሁሉ ድህነታችን ውስጥ ውብ ሰላም አለና በጥቁረት ውስጥ የተቀመጠ ሰላማችንን እንመልከት ነው ! ቡድንተኛ አንሁን ደካሞችን አናጥቃ ! የሸት ፉከራ ሽለላ ወንዝ የማይሽእገር ትህትናችንን ሁሉ የክፋታችን መሸፈኛ አናድርገው ነው !

ይህ ግለሰቦችን የማግለል ሃሳብ ዛሬ እንደፋሽን ያነሳሁት አይደለም ዶ/ር አሸብር በሚለው መጽሃፌ ላይ ማህበረሰቡ አምጾ ያገለላቸው ግለሰቦች ታሪክ ዋናውን ቦታ ይይዛል ! በዙቤይዳ መጽ ሐፊም እንደዛው ! ግለሰብ ለግለሰብ ካልተከባበርን አገር ላም አለኝ በሰማይ ነው! ምናልባት አንድ ብሔር ይዞ በመገንጠል ነጻነት ይገኛል በሎ የሚያስብም ካለ እውነታው ወዲህ ነው እንኳን መገንጠል እንደሽንኩርት ብንከተፍ ራሳችን ውስጥ ካለው ጨቋኝ አግላይና ከፉ ስብዕና አንላቀቅም በብሔር ሳይሆን በግል ነው ችግራችን! እ ያ ን ዳ ን ዳ ች ን !!

በጥላቻ ለደከምች ለታመመች ለመኖሪያ ስጋት ለሆነች አገራችን የነብስ አድን ጥሪ ይዘንላት የምንቆመው መፍትሄ እንቆጳዊነት ነው ! ገፉኝ ማለት ሳይሆን ማንንም አለመግፋት ግለሰብንም ይሁን ማህበረሰብ ! እንቆጳዊነት ይሄው ነው ራስን ማየት ራስን መቻል ሸክምን ከሌሎች ላይ ማንሳት ሁሉም የራሱን ሸክም በየጓዳው መሸከም! እንቆጳዊነት ማህበረስቡ የከመረው ቆሻሻ ክምር ላይ ቁሞ የማን ቆሻሻ ብዙ እንደሆነ መጠቆም ሳይሆን ከክምሩ ላይ የራሳችንን ቆሻሻ ማንሳትና ከተከመረ የቆሻሻ ተራራ ስር ሊኖር የሚመጣውን ትውልድ መታደግ ነው!!

ዘመቻችንን ጨርሰናል !!

find us on twitter.com/abulaGPAN

Afrikan Republic République africaine የአፍሪቃ ሪፐብልክ

www.gpanreunification.org

%d bloggers like this: